Friday, November 26, 2010

ግጥም ስናጣጥም Enjoying Amharic poetry

ገጣሚ፡- ገብረ ክርስቶስ ደስታ           

(መንገድ ስጡኝ ሰፊ፣ ገጽ 62)

የዓለም መራራነት

ያለም መራራነት ነው የሚጣፍጠን
መቸ መጣፈጧ፤
ኮሶውን በማሯ ጠቅልላ ስትሰጠን
        ስትሰጠን እሳቱን
አመድ አስመስላ ሸፍና ረመጡን፡፡
ስትሰጥ ማየ ሕይወት ስትሰጠን መድኃኒት
መርዟ ጨምራበት፡፡
ስትሰጠን እሬቱን ስኳር አስመስላ
እንደጎመን ሠርታ ሳማዋን ስንበላ፡:
                                
                                እሷ ትዞራለች
                                ፀሐይ ትሞቃለች
እኛን በብርድ ላይ በጨለማ ጥላ፡፡
ያለም መራራነት
የሚያቆራምድ ነው፤ የሚያኮራምት፡፡
ስትወስድ ወደኋላ ስትወስድ ወደ ሌላ
ምሥጢር ያላት መስላ፡፡
ከቤተሰብ ማሕል
ሰው ስታስኮበልል፡፡
ስትወስድ ስጦታዋን
ለገጸበረከት ያቀረበችውን፡፡
ሌባ ናት ሰራቂ
ቀጣፊ ነጣቂ፡፡
አቀባባይ ቀልማዳ፤ አታላይ አስመሳይ
ዋሾ ናት ወላዋይ፡፡
ሰው ሊኖር ባለም ላይ መች ተፈጠረ!
መንገደኛ እንግዳ
መሽቶበት የመጣ
ሠራተኛ አገልጋይ ነው የተቸገረ፡፡
ብዙ ነው ልፋቱ
ሲፈጠር፤ ሲመጣ፤ ሲወጣ ከቤቱ፡፡
አይችልም መዝናናት
በደመነፍስ ባሕርይ እንደተቀረጹት፡፡
እንዳህያ እንደጅብ ወይም እንደጦጣ
ወይም እንዳንበጣ
የማይቸገሩት ለምን ያስባሉ?
ከብቶች ይግጣሉ፤ ወፎች ይዘፍናሉ
አበቦች ያድጋሉ፡፡
ውስጡን አላወቁም፤ አልተመራመሩም
ሲመጡ ወዳለም፡፡
የውሸት ሥዕል ናት
                                ለዛዋ እሚጠፋ ቀለሟ እሚጠፋ፡፡
ጠረኗ እሚያባርር፤ ጣሟ እሚከረክር
ቧልቷ የሚያስመርር፡፡
የሰው ልጅ አንድ ባንድ ልታንሸራሽረው
ሁልጊዜ እንግዳ ነው
ማናፈስ ማቅበጧ
ማቻኮል ማሮጧ፡፡
ያለም መራራነት ነው የሚጣፍጠን
                                መቸ መጣፈጧ! 





የግጥም ልክፍተኛው ወዳጄ ሲሳይ ጫን ያለው ሬድዮ ፋና ላይ “ግጥም እናጣጥም” የሚል ድንቅ ዝግጅት ይዞላችኋል፡፡


By the way,
I got the pictures from the internet.
The man on the photograph is Gebrekirstos himself. The title of the painting below the poem is Patriots. <the3rdman.com>