መልካም መሬት
የእግዚአብሔርን ደስታ መጋራት!
ሐዋርያዊ ክርስትና ከሌሎች ፍልስፍናዎች ከሚለይባቸው አንዱ ነጥብ ለፍጥረት ያለው በጎ አተያይ ነው። ምሥራቃውያንም ምዕራባውያንም ፍልስፍናዎችና ሃይማኖቶች ተራቀቅን፣ መንፈሳዊ ኾንን ሲሉ ቁሳዊውን ዓለምና ተፈጥሮን ክፉ፣ የአማልክት ድብድብ ውጤት፣ ወይም ውስንነት፣ አለመቻል አድርገው ይመለከቱታል። ለምሳሌ፣ በPlatonic እና Pythagorean ፍልስፍና ሥጋ የነፍስ እሥር ቤት ነው። ይኽ ፍልስፍና ኋላ ላይ በ[ግ]ኖስቲኮችና በማኒቄያውያን በኩል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊገባ ሞክሮ፣ ብዙ መጻሕፍትን በሐዋርያት ስም እየጻፈ ሐዋርያዊ ያልኾኑ ትምህርቶችን አራብቶ ነበረ። ቅዱስ መኾን የሚቻለው በመተጣጠብ፣ የተለየ ልብስ በመልበስ፣ ቅጠላ ቅጠልና ፍራፍሬ ብቻ በመመገብ፣ አካልን የሚያስጨንቁ እጅግ ከባድ የኾኑ የትሕርምት (ascesis) ሥርዓቶችን በማከናወን እንደኾነ አድርጎ ማሰብ ተጀምሮ ነበረ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፣ እንደቅዱስ ሔሬኔዎስ ዘልዮን (137 እስከ 200ዓ.ም. የኖረ አባት)፣ እንደ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ ያሉ ብርቱ አባቶች በብዙ የትምህርት ተጋድሎና የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና በመሥራት ተከላክለውታል።
አበው ይቃወሙት ከነበረው የግኖስቲኮች አስተምህሮ መካከል አንዱ ፍጥረትን የሚያንኳስሰውን፣ ሥጋን የሚያናንቀውን “ፍጥረት የትንሣኤ ክብር ሊለብስ አይችልም” የሚል አመለካከትን ነበረ። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊጡርጊያ አመክንዮ ዘሐዋርያት በተሰኘው የሃይማኖት መግለጫ “እኛስ ጋብቻ ንጹሕ እንደኾነ መውለድም ርኩሰት እንደሌለበት እንናገራለን፤ ሕዝቡ ይበዙ ዘንድ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ፈጥሯቸዋልና” በማለት ይኽንኑ የፍጥረትን በጎነት ያውጃል። ይኽም በኦሪት ዘፍጥረት ላይ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ኹሉ አየ፤ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” ያለውን የሚያስተጋባ ነው። ፍጥረት መልካም ነው። በባሕርዩ አስቀያሚ ወይም መጥፎ ፍጥረትም የለም። ስለዚኽም ፍጥረትን ምክንያት አድርጋ ቤተ ክርስቲያን አምላኳን ታመሠግናለች። ክረምት ሲኾን “የዝናብ ኮቴው ተሰማ፤ ዝናብ ሲዘንብ ድኾች ይጠግባሉ” ፣ ዝናቡ ሲያልፍ ደግሞ “ዝናብ አለፈ፤ በረከት ቆመ፤ አበቦች አበቡ” እያለች ትዘምራለች። ይኽ ዝማሬ ያ በፍጥረት መጀመሪያ የተሰማው እግዚአብሔር በፍጥረት መገኘት ያወጀው “וְהִנֵּה־ט֖וֹב מְאֹ֑ד” (“እነሆም እጅግ መልካም ነበረ”) የሚለ ደስታ ማሚቶ (echo) ነው። የፍጥረትን መልካምነት እያወጀች የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ ደስታ ታስተጋባለች። የእግዚአብሔር ደስታው ይጋባብን ዘንድ በዝማሬ ትጋብዛለች። በምንባባትም ፍጥረትን ተመልክተን ራሳችንን እንድናይ ታሳስበናለች። የዛሬ ምንባባት ስለዘር (1ቆሮ 15)፣ ስለዝናብ (ያዕ 5)፣ ስለፍሬ (ሉቃ 8) የኾኑትም ለዚኽ ነው።
በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን የሚጠብቁ
ቃሉን የሚሰሙ ሰዎች በግሪኩ የተገለጹበት ቃል κατεχουσιν (ካቴኾውሲን) ይላል። ይኽም κατηχούμενος (ካቴኹሜኖስ) ከሚለው ንዑሰ ክርስቲያን ከሚጠሩበት ቃል ጋር ተዛማጅ ነው። የኹለቱም ሥራቸው κατέχω የሚል ቃል ሲኾን ትርጉሙም መያዝ፣ ማቆየት ነው። ሰዎች ከመጠመቃቸው በፊት የሚማሩትን ቃል በሚሰሙበት ጊዜ መስማታቸው መጠበቅን ዓላማ ያደረገ እንዲኾን የሚያሳስብ ቃል ነው። ክርስቲያን የመኾን የመጀመሪያው ነጥብ ባለ መልካም ልብ መኾን ነው። መልካም ልብ የሚባለው ደግሞ መልካም የኾነውን ነገር የሚፈቅድ፣ መልካምነትን የሚሻ፣ በመልካም ነገርም ደስ የሚለው ልብ ማለት ነው። መልካምን ነገር በእውነት ይፈልጋልና መልካም ልብ መልካም ዘር የኾነውን የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰማ ደስ ይለዋል። መልካም ስለኾነም መልካምን ነገር ሲያገኝ አጥብቆ ይይዘዋል። ይከተለዋል። ያገለግለዋልም። ለዚኽ ምሳሌ እንዲኾን የተዘረዘሩትን የጌታ ሴት ደቀ መዛሙርት መመልከት ይቻላል፦ “ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፣ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት ማርያም፣ የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና ብዙዎች ሌሎችም በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበረ።” መልካምን ይፈልጉ ነበረ። መልካምን አገኝዋት። እነሆ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የተገለጠችውና የቀመሷት የእግዚአብሔር መልካምነት እንዳትለያቸው በእግር ተከተሏት። መልካም ልብ ያላቸው ሰዎች መልካምን ሲያገኙ ይጠብቋታል። በውስጧ የተዘራውን መልካም በትኩረቷ ትይዘዋለች። የኅሊና ዋና ትኩረት በአላፊ አግዳሚ ወሬና ሰሞነኛ ዜና አይበታተንም። የተቀበለችውን መልካም በመንገደኛ ሐሳብ አታስረግጥም፤ መልሕቅ በሌላቸው ቶሎ መጥተው ቶሎ በሚበርሩ ሰሞነኛ ወፎችም አታስበላም። መልካም ልብ መልካምን ይፈልጋል። ሲያገኛትም አጥብቆ ይይዛታል። የያዛት መልካሚቱ የእግዚአብሔር ቃልም በውስጡ ታፈራለች። መልካም ምድር ዝናብን ጠጥታ እንደምታፈራ እርሱም እንዲኹ መልካምን በሕይወቱ ያፈራል። (እዚኽ ላይ፣ ሰዎች መልካም የሚሉትን፣ እርሱ መልካም የሚመስለውን አለማለቴ ይሠመርበት። መልካም የእግዚአብሔር ብቻ ነውና።)
በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ
መልካሙን ቃል አጥብቆ መያዝ ግን የሚያስከፍለው ዋጋ አለ። መልካሙ መሬት ምንም እንኳ የተዘራበትን ዘር ቢይዝም እንደወፎች በኾኑ ሰሞነኛ አስቸኳይ ጉዳዮች ሐሳቡን ለመበታተንና መልካሙን ዘር ከመልካሙ ልብ ለመንጠቅ መሞከራቸው አይቀርም። ስለዓለም የመጨነቅና ምቾትን የማምለክ ሐሳብ እሾኽም ለመብቀል መሞከሩ አይቀርም። ስለዓለም የከረረው የመከራ ፀሐይም መውጣቱ አይቀርም። ወፎቹ ማረፊያ ቦታ እንዳያገኙ በጸሎት የማባረር፣ እሾኹም በቅሎ መልካሙን ዘር እንዳያንቀው የየዕለት ንስሐ የሚባል የአረም ሥራ ይፈልጋል። መልካሙ ቃል በኑሮ ሲገለጥ ፈተና ከሚያውቁንና ከምንወድዳቸው ሰዎች፣ ወይም ከማያውቁንና ስለእኛ ግድ አላቸው ብለን ከማናስባቸው ሰዎች ወይም በራስ ወዳድነት ላይ ከተመሠረተው የማኅበረሰብ የአኗኗር ሥርዓት የሚመጣ ሥር የሌላቸውን የማድረቅ ዐቅም ያለው የመከራ ፀሐይ ይወጣል። ሥር ያላቸው ግን ፍሬ ማፍራት የጀመረውን መልካሙን ዘር የማያቋርጥ የሕይወት ውኃ የኾነው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ከሚፈስስባት ቤተ ክርስቲያን ራሳቸውን ይተክላሉ። በቃሉ ላይ ተመሥርተዋልና ወጀብም ዐውሎ ነፋስም አያናውጣቸውም። ይልቁን ዕለት ዕለት የመጀመሪያውን ዘር አጥብቀው ይይዙ ዘንድ ሥራቸውን በወንዙ ዳርቻ አስፍተው ይዘረጋሉ። ከቅዱስ ቃሉ አይለዩም። ከቅዱሳት ምሥጢራት አይለዩም። የያዙትን የሚጸኑበትም በዚኽ ነው። ቅዱሳት አንስት ቃሉን ሰምተው ጌታን እንደተከተሉት እነርሱም ቃሉን ሰምተው በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ከሚኖረው ክርስቶስ አይለዩም።ጥዑም ቃሉን የሰሙትን ጌታ፣ ዕለት ዕለት በቅዱሳት ምሥጢራት ያጣጥሙታል፤ ከኃይል ወደ ኃይል ይኼዳሉ። በጎው ቃል በውስጣቸው ያስተጋባልና በጎ ለመሥራት ይወጣሉ። ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶ ያማረ በጎ ሥራ ይሠራሉ። በመሥራታቸውም አይታክቱም። እንዳያፈሩ የሚፈታተናቸውን እባቡንና ጊንጡን እየረገጡ ይኼዳሉ። አይደክሙምም። ጌታም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉ ናቸውና “እናቴ፣ ወንድሞቼ” ብሎ ይጠራቸው ዘንድ አያፍርም።
ጥያቄ፦ እኔ ለቃሉ በጎ መሬት ነኝ ወይ? ቃሉንስ እይዛለኹ ወይ? ቃሉ በእኔ ላይ በጎ ሥራን አፍርቷል ወይ? ቃሉ እንዲያፈራ ከእውነተኛው የሕይወት ውኃ ክርስቶስን በቅዱሳት ምሥጢራት እየተመገብኹት ነው ወይ?
No comments:
Post a Comment